ጊፍት ሪል ስቴት ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመረቁ

ጊፍት ሪል ስቴት ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመርቀዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ አምስት ወለሎች ያሉት ሲሆን እስከ 70 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከለሚ ኩራ ክፍለከተማ በቀረበው ጥያቄ መሰረት ቤቶችን ለማጠናቀቅ ሁለት ወራት ብቻ ወስዷል፡፡

ጊፍት ሪል ስቴት ከእህት ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከነዚህ ማህበራዊ ኃላፊነቶች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን÷ በመዲናዋ ለሚኩራ ክፍለከተማ የተገነቡ 40 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የጊፍት ሪል ስቴት ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ ለግንባታው ተገቢውን ትኩረት በመስጠት 24 ሰዓታት ያለምንም እረፍት በመሰራቱ በውሉ መሰረት በሁለት ወራት ውስጥ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው አያይዘውም በግንባታው የተሰማሩ አካላት ባደረጉት ያላሰለሰ ክትትልና ቁጥጥር ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ እገዛ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

ይህም የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን አቅም እያደገ መምጣቱ ማሳያ መሆኑን አቶ ገብረየሱስ ገልጸው ለሌሎች ኮንትራክተሮች ምሳሌ ይሆናል ብለዋል፡፡

ጊፍት ሪል ስቴት በሽያጭ ከሚያቀርባቸው የተለያዩ ቤቶች ባሻገር የቤት እጥረትን ለመቅረፍ ለአቅመ ደካሞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ገብረየሱስ ገልጸዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *