ታላቁ የአድዋ ድል!

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው … በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡

ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ፡፡

ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፤ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡

ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል (የአድዋ ድል) በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቶአል፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች በአድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፡- ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ የተባሉት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ) የአፍሪቃና የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመረጡ፡፡

ይሄ (በአውአሎም ብስለትና ሥልጡንነት መስዋዕትነትና ኢትዮጵያዊ ፍቅር የተገኘው) ሰለጠነ በሚባለው የአውሮጳ ኃይል ላይ አልሰለጠነም በሚባለው አፍሪቃዊ ኃይል የተጨበጠ ትልቅ የወታደራዊ መረጃ (Military Security intelligence) ብልጫ ወይም ድል ነው፡፡

በዚህም ዲፕሎማሲያዊ ሥልጣኔዋን ለመላው አውሮጳ እና ለመላው ዓለም በተጨባጭ አሳየች፡፡ ከመቶ ዓመታት በላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛ አፍሪቃዊት አገር፡- ኢትዮጵያ ነች፡፡ የአብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ከስድሣ ዓመት አይዘልም፡፡ ኢትዮጵያ፡- ከኢጣሊያና ከፈረንሣይ ከአሜሪካ (USA) እና ከእንግሊዝ ከሩሢያና ከጀርመን (ከስድስት አገራት) ጋር ከመቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አዳብራ እና አፅንታ ቆይታለች፤ በአድዋ ድል፡፡

የአድዋ ድል በጦር ግንባር ፍልሚያ የተገኘው ዋነኛው ድል ነው፤

ታላቁ የአድዋ ድል!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *